ሐዋርያት ወንጌሉን በመጀመሪያ በቃል ከሰበኩ በኋላ ያንኑ ወንጌል በጽሑፍ ካስተላለፉ፣ በሐዋርያት የተነገረውና የተጻፈው ቃል አንድ ዓይነት መለኮታዊ ሥልጣን የላቸውምን?
By Super Admin
ሐዋርያት ወንጌሉን በመጀመሪያ በቃል ከሰበኩ በኋላ ያንኑ ወንጌል በጽሑፍ ካስተላለፉ፣ በሐዋርያት የተነገረውና የተጻፈው ቃል አንድ ዓይነት መለኮታዊ ሥልጣን የላቸውምን? በእርግጥም ሁለቱም እኩልና አንድ ዓይነት ፍጹም ሥልጣን (co-equal and identical authority) አላቸው፤ ምክንያቱም የሁለቱም መገኛ እና የማንቀሳቀሻ ምክኒያት (efficient cause) እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ይህንን እውነት ቀጥሎ ባለው መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ ማስረጃ እናረጋግጣለን። ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ በሁለተኛ መልእክቱ ላይ፦ " ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም። ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል። " በማለት ይናገራል። [፪ ጴጥሮስ ፩፥፲፪-፲፫] በመቀጠልም በዚህ ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንደማይቆይና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገለጠለት ይህንን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥሎ እንደሚሄድ (ማለትም በሰማዕትነት እንደሚያርፍ) ይገልጻል። እንግዲህ ሐዋርያው ከእነርሱ ከተለየ በኋላ ዘወትር ማን ሊከታተላቸውና ሊያሳስባቸው ይችላል? ለዚህ ነው ሐዋርያው ቀጥሎ፦ " ከሄድኩም በኋላ እነዚህን ነገሮች ዘወትር ታስቡ ዘንድ እተጋለሁ " የሚለው። [፪ ጴጥሮስ ፩፥፲፭] ሐዋርያው በአካል በሌለበትና ከዚህ ዓለም በተለየበት አውድ ውስጥ ምእመናን "ዘወትር" ይህንን እውነት ማሰብ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህ ሊሆን የሚችለው ሐዋርያት የተናገሩትን ሕያው ቃል በማይለወጥ ጽሑፍ (in scripto) አስቀምጠውላቸው ሲሄዱ ብቻ ነው። ለዚህም ነው ጴጥሮስ በዚያው መልእክቱ ላይ የምእመናንን ንጹሕ ልቦና ለማነቃቃት ሲል፥ በቅዱሳን ነቢያት አስቀድሞ የተነገረውን ቃልና በሐዋርያቶቻቸው አማካኝነት የተሰጠችውን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንዲያስታውሱ ይህንን ሁለተኛ መልእክት እንደጻፈላቸው በግልጽ የሚናገረው። [፪ ጴጥሮስ ፫፥፩-፪] ከዚህ የምንረዳው፥ ሐዋርያቱ በቃል የሰበኩት (preaching/kerygma) እና በጽሑፍ ያስቀመጡት (Scripture/graphe) ሁለት የተለያዩ የሥልጣን ደረጃዎች የሌሏቸው መሆኑን ነው። ሁለቱም እኩል መለኮታዊ ሥልጣን አላቸው፤ ምክንያቱም በቃል ሲናገሩም ሆነ በጽሑፍ ሲቀዱ ይመሩ የነበሩት በአንድ መንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት (divine inspiration / θεοπνευστία) ነው። ሐዋርያቱ በአደባባይ የተናገሩትን ያንኑ ንጹሕ ወንጌል ለትውልድ ማቆያ ይሆን ዘንድ በጽሑፍ እንዳስተላለፉልን የሐዋርያት ደቀ መዝሙር የሆነው የፖሊካርፕ ተማሪ ቅዱስ ኤሬኔዎስ (St. Irenaeus of Lyons) በታዋቂው «በክህደት ላይ የተሰጠ ምላሽ» (Against Heresies / Adversus Haereses) መጽሐፉ ላይ እንዲህ በማለት በግልጽ ያትመዋል፦ " ከእነዚያ ወንጌል ወደ እኛ ከደረሰባቸው ሰዎች በቀር የመዳናችንን ዕቅድ (oeconomia salutis) ከሌላ ከማንም አላወቅንም። እነርሱም በመጀመሪያ በሕዝብ ፊት ሰበኩት፤ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ የእምነታችን መሠረትና ምሰሶ (fundamentum et columnam fidei nostrae) እንዲሆን በቅዱሳት መጻሕፍት ለእኛ አስተላለፉት። አንዳንዶች ራሳቸውን ከሐዋርያት የተሻሉ አድርገው እየቆጠሩ፣ ሐዋርያት ፍጹም እውቀት ከማግኘታቸው በፊት እንደሰበኩ ለመናገር ይደፍራሉ፤ ይህን አባባል መናገር ግን ኃጢአት (ክልክል) ነው። ምክንያቱም ጌታችን ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በወረደ ጊዜ ከላይ ኃይል ተቀበሉ፤ በሁሉም ስጦታዎቹ ተሞሉ፣ ፍጹምም እውቀት (perfectam agnitionem) አገኙ። ከዚያም ወደ ዓለም ዳርቻዎች ሄደው ከእግዚአብሔር ለእኛ የመጡትን መልካም ዜናዎች ሰበኩ፣ ለሰዎችም የሰማይን ሰላም አወጁ፤ እያንዳንዳቸውና ሁሉም በአንድነት የእግዚአብሔርን ወንጌል በሙላት ይዘው ነበርና። ጴጥሮስና ጳውሎስ በሮም ሲሰብኩና የቤተ ክርስቲያንን መሠረት በሚጥሉበት ጊዜ፣ ማቴዎስም ለዕብራውያን በራሳቸው ቋንቋ ወንጌሉን በጽሑፍ አወጣ። እነርሱም ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላ (post horum discessum)፣ የጴጥሮስ ደቀ መዝሙርና ተርጓሚ የነበረው ማርቆስ፣ ጴጥሮስ የሰበከውን በጽሑፍ ለእኛ አስተላለፈ። ለጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ የነበረው ሉቃስም በእርሱ የተሰበከውን ወንጌል በመጽሐፍ አስቀመጠ። ከዚያም በኋላ በጌታ ደረት ላይ የተደገፈው የጌታ ደቀ መዝሙር ዮሐንስ፣ በእስያ በኤፌሶን በሚኖርበት ዘመን ራሱ ወንጌሉን አወጣ። [እነዚህ ሁሉ] የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነ አንድ አምላክ እንዳለ፣ በሕግና በነቢያትም የተነገረውን፣ እንዲሁም አንድ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንዳለ አስታውቀውናል። ማንም ሰው ከእነዚህ እውነቶች ጋር ካልተስማማ፣ የጌታን ባልንጀሮች ይንቃል፤ ከዚህም በላይ ጌታውን ክርስቶስን ይንቃል፤ እንዲሁም አብን ይንቃል። እርሱ ራሱን በራሱ ይኰንናል፣ የራሱንም መዳን ይቃወማል፤ ይህም በሁሉም መናፍቃን ዘንድ እንደሚታየው ነው። " በክህደት ላይ የተሰጠ ምላሽ (መጽሐፍ ፫፣ ምዕራፍ ፩) ስለዚህ፣ ሐዋርያቱ በአካል እየተዘዋወሩ የሰበኩትን ያንን መለኮታዊ እውነት፣ እኛ ዛሬ ያለ ምንም መበረዝ እንድናገኘው በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በቋሚነት አስቀምጠውልናል። በዚህም መሠረት የሐዋርያት የቃል ስብከትና የሐዋርያት የጽሑፍ መልእክት ሁለቱም የአንድ መለኮታዊ ወንጌል መግለጫዎች በመሆናቸው እኩልና የማይናወጥ ሥልጣን እንዳላቸው በዚህ ፍጹም አድርገን እናጸናለን።