ቤተክርስትያን ከመጽሃፍ ቅዱስ ትቀድማለች ለዚያ እስዋ የበላይ ባለስልጣን ነች?

By Milkiyas

ቤተክርስትያን ከመጽሃፍ ቅዱስ ትቀድማለች ለዚያ እስዋ የበላይ ባለስልጣን ነች?

በመጀመሪያ የዛሬው ክታብ መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ እራሱ ምን እንደሆነ አያብራራም። ብዙ የሃገራችን ኦርቶዶክሳውያን እናም በአጠቃላይ "ecclesialists" የመጽሃፍ ቅዱስ ብቻ አስተምህሮ አረዳዳቸው ከአንድ ምዕመን ወይም እንዲሁ ከራሳቸው ምልከታ እንጂ እኛ በራሳችን ሊቃውንቶች በገለጽነው መሰረት ስላልሆነ ችግር ቢፈጥርም ለዛሬ ግን ይህን ታዋቂ ተቃውሞ እንመልከት።

የሚታወቅም አባባል አላቸው፡ "ከሙሴ በፊት መጽሃፍ ቅዱስ አልነበረም፣ ነገር ግን ከሙሴ በፊት ቤተክርስትያን ነበረች"። እና ምን ይሆን መልሳችን፣ እውን መልስ ሳይኖረን ነውን?

ምልከታ 1

መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ ስንል በሌላ አገላለጽ እያልን ያለነው የእግዚያቢሄር ቃል ብቻ እንደማለት ነው። የእግዚያቢሄር ቃል ደሞ በዚህ ዘመን ምንም እንከን በሌለበት መልኩ ፍጹም ሳይሳሳት የተላለፈው በመጽሃፍ ቅዱስ ብቻ እንደመሆኑ የእግዚያቢሄር ቃል ብቻ የሚለው ምልከታ መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ ለማለት ያስገድዳል። ይህን ካልን፣ ቤተክርስትያን ከእግዚያቢሄር ቃል ትቀድማለች እንዴ? በፍጹም!! ቤተክርስትያን ሁሌም የምትመሰረተው በእግዚያቢሄር ቃል ነው። ከሙሴ በፊት የነበረችው ቤተክርስትያን የተመሰረተችው እግዚያቢሄር ለአብራሃም ባስተላለፈው ቃልኪዳን ነው፣ የአዲስ ኪዳንዋም ቤተክርስትያን እንዲሁ። ለዚያ ቤተክርስትያን ምትቀድመው የእግዚያቢሄር ቃል ከመጻፉ ነው እንጂ ከራሱ ከእግዚያቢሄር ቃል አትቀድምም።

በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው፤ '

ኤፌሶን 2:20

ምልከታ 2

እስቲ ለሙግቱ ብለን ቤተክርስትያን ትቀድማለች ብለን እንውሰድ ለሙግቱ ጥቅም ብለን። ታድያ የሆነ ነገር ቀድሞ መምጣቱ መጪው ነገር ላይ በላይ ወይም ገዢ ወይም ደሞ የበለጠ ስልጣን ይሰጠዋልን? በፍጹም !!ህግ ከወንጌል ይቀድማል፣ ታድያ ህግ ከወንጌል ይልቃልን? መጥምቁ ዪሃንስ ከክርስቶስ ይቀድማል፣ ታድያ መጥምቁ ዩሃንስ ክርስቶስ ላይ ስልጣን አለውን?

ይሄ ሙግት ፍጹም ደካማ እንደሆነ እንገነዘባለን፣ ለዚያ አሁንም እስከለተሞታችን ድረስ ለእምነትና ልምምድ ብቸኛ ማይሳሳተው ባለስልጣን፣ የሁሉነገራችን መዛኝ እንደሆነ እየመሰከርን እንሞታለን!!