መጽሃፍ ቅዱስ ግልጽ ቢሆንማ ፕሮቴስታንት ቤተክርስትያን ውስጥ አስተምህሮዋዊ ልዪነቶች አይኖሩም ነበር፣ ነገር ግን አስተምህሮዋዊ ልዪነቶች ስላሉ ይህ ማለት መጽሃፍ ቅዱስ ግልጽ አይደለም!

By Milkiyas

መጽሃፍ ቅዱስ ግልጽ ቢሆንማ ፕሮቴስታንት ቤተክርስትያን ውስጥ አስተምህሮዋዊ ልዪነቶች አይኖሩም ነበር፣ ነገር ግን አስተምህሮዋዊ ልዪነቶች ስላሉ ይህ ማለት መጽሃፍ ቅዱስ ግልጽ አይደለም!

አጭር ምላሽ

ይሄ ሙግት እንደ ቅድመ እሳቤ የወሰደው አንድ ነገር አለ፣ ይህም የአረዳድ ወይም ትርጓሜ ልዪነቶች የሚኖሩበት ብቸኛ ምክንያት እየተተረጎመ ያለው ነገር ግልጽ ካልሆነ ብቻ ነው የሚል ነው። ይሄ ደሞ ፍጹም ስህተት የሆነ ቅድመ እሳቤ ነው፣ የሆነ ነገር ግልጽ ሆኖ ሳለ ራሱ የአረዳድ እና ትርጓሜ ልዪነቶች አሉ፣ አንዳንድ ምሳሌ እንመልከት፡

1) የፈጣሪ መኖር። ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 1 እንደገለጸው የአምላክ መኖር በግልጽ ያለ ድርድር ሁሉም ሊያየው የሚችል መሠረታዊ እውነት ነው። ነገር ግን ብዙ ኢ-አማንያን አሉ። ታድያ ይህ ማለት የእግዜር መኖር ግልጽ አይደለም ማለት ነው?

2) ሁለት ጾታ ብቻ መኖር፡ ለ2000 አመት ሁሉም ሰው እንደ ቅድመ እሳቤ ሲወስደው የኖረው እውነት ነው፣ ይህም የሰው ልጅ ወንድና ሴት ጾታ እንዳለው። ነገር ግን በዚህ ዘመን በምዕራቡ አለም እንደምናቀው አይ ወንድ ሴት ሚባለው ነገር ማህበረሰቡ የፈጠረው "gender" ነው እና ከሁለት በላይ ጾታ አለ፣ ጾታ ሊለወጥ የሚችል ነገር ነው ብለው የሚያስቡ በጣም በርካታ የተማሩ ሰዎች አሉ። ታድያ ይሄስ እኛና እነሱ ስለተለያየን ይህ ማለት ሰው ልጅ ሁለት ጾታ ብቻ እንዳለው ግልጽ አይደለም ማለት ነው?

ፈጣሪ ለመኖሩ ያለው ማስረጃም ሆነ የሁለት ጾታ ብቻ የመኖር ማስረጃ በጣም ግልጽ ነው። ነገር ግን ሰዎች በራሳቸው ቅድመ እሳቤዎች፣ ምኞቶች ወዘተ ማስረጃውን በመተው ማስረጃውን እንደኛ አልተረጎሙትም(ምንም እንኳን ማያሻማ ቢሆንም)።

ይሄ ደሞ በመንፈሳዊ አለም ሲመጣ ምንኛ የበለጠ እውነት ነው? እኛ አዳማዊ ባህሪ ያለብን ሰዎች፣ ፍጹማን ያልሆንን ሰዎች ቅዱሳት መጻህፍትን በራሳችን ቅድመ እሳቤዎች፣ በራሳችን ልብ ባላልነው ምኞቶች(ልብን ማን ያውቃታል ማን ይመረምራታል ይላል መጽሃፍ) ወዘተ ምክንያት ቅዱሳት መጻህፍት አጣመን ልንረዳ አንችልም? ይሄ እውን ከመጽሃፍ ቅዱስ ግልጽነት የሚጋጭ እውነት ነውን?

ወደ አባቶች ትምህርት እንመለስ፣ በዘመናት ከኖረችው ቤተክርስትያንና ቅዱሳን ጋር አብረን ቅዱስ ቃሉን ከፍ አርገን ለድህነት የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደያዘ እና ይህንንም በግልጽ እንዳስነበበን አብረን እንመስክር።