ጴጥሮስ ዋልዴስ

ጴጥሮስ ዋልዴስ

By Augsburg Catholic

ጴጥሮስ ዋልዴስ

በአሥራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ሊዮን በተባለው የደቡብ ፈረንሳይ ከተማ ጴጥሮስ ዋልዴስ የተባለ አንድ ሀብታም ነጋዴ ይኖር ነበር።

በመጀመሪያ በምድራዊ ሀብቱ ከመጠቀምና ከመደሰት በስተቀር ሌላ ነገር አስፈላጊ መስሎ ስላልታየው፤ ስለ እግዚአብሔር ወይም ስለ ነፍሱ ደኅንነት እምብዛም አያስብም ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ግን አንድ ዘማሪ በመንገድ ዳር ቆሞ መንፈሳዊ መዝሙር ሲዘምር ሰማ። በመዝሙሩም ቃል ልቡ እጅግ ስለተነካ እስከ አሁን የነበረበት የኑሮ ከንቱነት ይታየው ጀመር። ከዚያም ንስሐ ለመግባት እግዚአብሔርንም ለመፈለግ ናፍቆት አደረበት። ያካበተው ገንዘብ የእግዚአብሔርን መንገድ እንዳይከተል እንቅፋት የሚፈጥርበት መስሎት ከምድራዊ ሀብቱ ተለየ። ግማሹን ለዘመዶቹ አካፍሎ ከሰጠ በኋላ ቀሪውን ለድሆች ለገሠ። ወንጌልንም ለመስበክ ሲል የእግዚአብሔር ድሀ ለመሆን ለራሱ ወሰነ። ለቃሉ መስፋፋት ይጠቅማል በማለት ሁለት ካህናት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፈረንሳይ ቋንቋ እንዲተረጉሙ ቀጠራቸው። ራሱም ቅዱሳት መጻሕፍትን በትጋት የሚያጠና ሰው ሆነ። ስብከትም ጀመረ። ትምህርቱንም በደስታ የሰሙትና የተቀበሉት እየበረከቱ ሄዱ።

ጴጥሮስ ዋልዴስ በሞት ከዚህ ዓለም የተለየው በ1217 ዓ.ም. ነው። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ተከታዮችን አግኝቶ ነበርና እርሱ የጀመረውን አገልግሎት እነርሱ ቀጠሉት።

የዋልዴስን አስተያየት በመደገፍ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ እንጂ በተላለፈልን በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት መመራት የለብንም ይሉ ነበር።

በሌሎችም በልዩ ልዩ የትምህርት ነጥቦች ላይ ከቤተ ክርስቲያን መለየታቸውን መግለጥ ግዴታ ሆነባቸው። ለምሳሌ እንደ ቤተ ክርስቲያን የጸጋ ምሥጢራት ሊባሉ የሚገባቸው ቅዱስ ጥምቀትና ቅዱስ ቍርባን ብቻ ናቸው በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ ሰባት የጸጋ ምሥጢራት የምታደርገውን ትምህርት ይቃወሙ ነበር። እንዲሁም፦ ከሞት በኋላ ነፍሳት የሚነጹበትና የሚፈተኑበት እሳት አለ የሚለውን፣ ደግሞ:- ለሞቱት ሰዎች ደኅንነት ተብሎ ቅዳሴን ማድረግ ይጠቅማል፤ ለነፍስ ደኅንነት ተብሎ ለቤተክርስቲያን ገንዘብን መስጠት መልካም ነው፤ ቅዱሳንንም ማምለክ ተገቢ ነው የሚሉትን የሮም ቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች እንደ ስሕተት አድርገው ይቆጥሩአቸው ነበርና አልተቀበሉም።

ለጸሎት በሚሰበሰቡበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ይነበባል። ስብከትም ይሰበካል። እንጀራ መቁረስም አለ፤ እግዚአብሔርንም ይለምናሉ። የእግዚአብሔርን ቃል ማስፋፋት ዓላማ አድርገው ስለ ተነሡበት ምክንያት በማኅበራቸው የተመረጡ የወንጌል መልእክተኞች ወደ ልዩ ልዩ አገር እየደረሱ ስብከት ያደርጉ ነበር። ሁለት ሁለት እየሆኑ በከተማ በገጠርም ያስተምሩ ነበር። በደረሱበትም አገር ሁሉ ሰውን ደስ ስላሰኙ ተቀባይነትን ያገኙ ነበር። የሮም ቤተ ክርስቲያን አልወደደቻቸውም። ካለመውደድም አልፋ እነዚያን ወንጌላውያን ለመጥላትና ለማሳደድ ተነሣች። በትምህርትዋ ያልተስማሙትን ለመቅጣት ባቋቋመችው ፍርድ ቤት እየተጠቀመች በዋልዴሳውያን ላይ ቀንደኞችዋን አሰለፈች። የማኅበሩም አባሎች ክፉኛ ተሰደዱ። በሚያሰቅቅ ቅጣት የተቀጡ፣ የሞትም ፍርድ ተፈርዶባቸው የተገደሉት በሺህና በሺህ የሚቆጠሩ ናቸው።

ይሁን እንጂ ከእምነታቸው ጽናት የተነሣ ዋልዴሳውያን አልተደመሰሱም። የዚህች ቤተ ክርስቲያን አባሎች የሆኑት ምዕመናን እስከ ዛሬ ይገኛሉ። በተለይ በኢጣልያ አገር የቤተ ክርስቲያናቸው አባሎች ብዛት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ነው።

- የቤተክርስቲያን ታሪክ በመካከለኛው ዘመን ዩሐንስ ሳንድቬድ

Comments

Log in to join the conversation.

Log In

No comments yet — be the first to share your thoughts.