የውሃ ጥምቀት ወይስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት?
By Pastor Josh Sullivan (translation:- Augsburg Catholic)
የውሃ ጥምቀት ወይስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት?
ጥያቄ ፡ ስለ ያልተጠመቁ ሰዎች የሰራኸውን ቪዲዮ አየሁ፣ እናም ጥምቀት አስፈላጊ እንደሆነ ስትናገር ሰማሁ። አሁን መንፈሳዊ ጥምቀት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት አስፈላጊ እንደሆነ አውቃለሁ፣ ነገር ግን አካላዊ ጥምቀትንም (በውሃ መጠመቅን) እየጠቀስክ እንደሆነ ለማወቅ ጓጉቼ ነበር። እኔ ቀድሞውኑ ተጠምቄያለሁ፣ ነገር ግን ጉጉት ስላደረብኝ ብቻ ነው የጠየቅሁት።
መልስ ፡ ከውሃ ጥምቀት የተለየ መንፈሳዊ ጥምቀት አለ የሚለው አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ሳይሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት የሚናገረውን ነገር ከመካድ የመነጨ ሐሳብ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን 4፡5 ላይ "አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት " ይላል። ቅዱስ ጳውሎስ የውሃ ጥምቀትን ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተቃራኒ የሆነና ከውሃ ጥምቀት ተለይቶ የሚመጣ አድርጎ በፍጹም አላስተማረም። አንድ ጥምቀት ማለት አንድ ጥምቀት ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያንም በኒቂያ የሃይማኖት መግለጫ ሦስተኛው አንቀፅ ላይ "ለኃጢአት ስርየት አንዲት ጥምቀት" እንዳለች ትመሰክራለች። "የውሃ ጥምቀትን" ብቸኛው ጥምቀት የሚያደርገው፣ ጥምቀት ውሃ ብቻ ስላልሆነ ነው። ውሃው ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ተዳምሮ ነው። ሉተር በትንሹ ካቴኪዝሙ ውስጥ በሚያምር መልኩ እንዲህ ይላል፦ "ያለ እግዚአብሔር ቃል ከሆነ ውሃው እንዲሁ ውሃ ብቻ ነው እንጂ ጥምቀትም አይደለም፤ ዳሩ ግን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ከሆነ ጥምቀት ይሆናል ፣ ማለትም ጸጋን የተሞላ የህይወት ውሃና "ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ " እንደ ተባለው ይሆናል፣ ይኸውም ቅዱስ ጳውሎስ ለቲቶ ሲጽፍ በምዕራፍ 3:5-8 "...ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነውበጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም ፣ ያን መንፈስም በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾችእንድንሆን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው::' ይህ በጣም እውነት ነው።" ስለዚህ ጥምቀት ተራ ውሃ ብቻ አይደለም። ከእግዚአብሔር ቃልና ተስፋ ጋር የተዳመረ ውሃ ነው፣ ስለዚህም መንፈስ ቅዱስ ተገኝቷል። ራሱ ኢየሱስ በዮሐንስ 3፡5 እነዚህን ሁለት ነገሮች እንዴት እንዳዋሃደ አስተውል፦ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። " ዳግም መወለድ፣ አዲስ ፍጥረት መሆን ፣ በመንፈስ ዳግም መወለድ የሚደረገው በውሃና በመንፈስ እንጂ ውሃና መንፈስ ተለያይተው አይደለም።
አንዲት ጥምቀትን ወደ ሁለት የሚከፍሉ የሚመስሉ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ፣ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በዐውዳቸው ሊፈቱ ይችላሉ። የመጀመሪያው የመጥምቁ ዮሐንስ በማቴዎስ 3፡11 ያለው ንግግር ነው። ዮሐንስ " እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤" ይላል። አንዳንዶች ይህንን ዮሐንስ በውሃ ብቻ ያጠምቃል፣ ኢየሱስ ግን በመንፈስ ቅዱስ እና በእሳት ያጠምቃል ብለው ይተረጉሙታል። ነገር ግን "በውሃ" የሚለው ሐረግ "በውሃ ብቻ" ማለት አይደለም። ዮሐንስ "በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል" ሲል ፈጽሞ ስለ ሌላ ነገር እየተናገረ ነው። ኢየሱስ ይህ የመንፈስ ጥምቀት ምን እንደሆነ በሐዋርያት ሥራ 1፡5 ላይ ይተረጉማል። ለሐዋርያት እንዲህ ይላቸዋል፦ " ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ::" በቁጥር 8 ላይ " ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ::" ይላል። ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስና የእሳት ጥምቀት በበዓለ ኀምሳ ቀን ለሐዋርያት የተሰጠው ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው።(ሐዋ 2:3)የእግዚአብሔርን ታላላቅ ሥራ (ሐዋ. 2፡11) ለማወጅ ተናገሩ። መጥምቁ ዮሐንስ የውሃ ጥምቀትንና ከዚህ የተነጠለ "የመንፈስ ጥምቀት"ን (ክርስቶስ የሚያመጣውን ማለት ነው) አላስተማረም። ተመሳሳይ ሁኔታ በሐዋርያት ሥራ 11፡15-16 ይገኛል። ጴጥሮስ ወንጌልን ለቆርኔሌዎስ ቤተሰብ ሲሰብክ "ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው። ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ።" በማለት ይተርካል። እንደገና ይህ "በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ" ክርስቶስ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ያለውን "የመለያየትን መካከለኛ ግድግዳ" (ልክ ቅዱስ ጳውሎስ ኤፌ. 2፡14 ላይ እንደሚለው)እንዳፈረሰ ለማሳየት የተደረገ ልዩ የመንፈስ መገለጥ ነው።
ውሃንና መንፈስን በጥምቀት ውስጥ ለመለያየት አንዳንዶች የሚጠቀሙት ሌላኛው ጥቅስ የኢየሱስ ንግግር በሉቃስ 12፡49-50 ነው። "በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ፥ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ? ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፥ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ?" ይላል። በዚህ የኢየሱስ አገልግሎት ወቅት እርሱ ቀድሞውኑ በዮሐንስ ተጠምቆ ነበር ስለዚህ እያወራ ያለው ያንን ጥምቀት አይደለም። እንዲሁም ኢየሱስ በድጋሚ ተጠምቆ አያውቅም። እዚህ የሚያመለክተው ጥምቀት የስቃዩና የሞቱ ምሳሌያዊ ጥምቀት ነው።
ሌላው ጥቅስ ሐዋርያት ሥራ 19፡1-6 ነው። በእነዚያ ቁጥሮች ጳውሎስ በኤፌሶን መንፈስ ቅዱስ ስለመኖሩ ምንም የማያውቁ ሆኖም በዮሐንስ ጥምቀት የተጠመቁ የተባሉ ደቀ መዛሙርትን ቡድን ያገኛል። ይህ የሚያሳየው በእውነት የዮሐንስን ጥምቀት እንዳልተቀበሉ ነው፣ ምክንያቱም ዮሐንስ እንደ ማርቆስ 1፡4 "የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት " ይሰብክ ስለነበር፣ ይህም ማለት መንፈስ ቅዱስ ኃጢአትን ለመደምሰስ በዮሐንስ ጥምቀት ውስጥ ተገኝቶ ነበር ማለት ነው። ዮሐንስ ያስተማረው "የሚመጣው" ደርሶ እንደሆነ ከነገራቸው በኋላ ጳውሎስ በኢየሱስ ስም ያጠምቃቸዋል፣ ይህም በማቴዎስ 28፡19 ላለው የሥላሴ ቀመር አጭር መጠሪያ ነው። ይህ ዳግም ጥምቀት አይደለም ምክንያቱም የመጀመሪያ ጥምቀታቸው እውነተኛው የዮሐንስ ጥምቀት ስላልነበረ ነው። ከዚያም፣ ይህ አስፈላጊ ነው፣ ጳውሎስ እጆቹን በላያቸው ላይ ጫነ ፣ በዚያም ወቅት መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ 2 ላይ በሐዋርያት ላይ እንደ ወረደ እና በሐዋርያት ሥራ 10 ላይ በቆርኔሌዎስና በቤተሰቡ ላይ እንደ ወረደ በእነርሱ ላይ ወረደ ። መንፈስ ቅዱስ በእርግጥ በጥምቀታቸው ውስጥ ተገኝቶ ነበር ምክንያቱም ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ 2፡38 የሚንስሐ የገባና የተጠመቀ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንደሚቀበል ስላስተማረ እና ኢየሱስ በዮሐንስ 3፡5 ዳግም መወለድ በውሃና በመንፈስ እንደሚመጣ ስለሚናገር ነው።
ከ"ውሃ ጥምቀት" የተለየ "የመንፈስ ጥምቀት" አለ የሚለው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ አይደለም። ሥሩ የተመሠረተው በስዊስ ተሃድሶ አራማጅ በኡልሪክ ዝዊንግሊ ሐሳቦች ላይ ነው። ዝዊንግሊ በ1530 በአውግስቡርግ ምክር ቤት (የአውግስቡርግ የሃይማኖት መግለጫ በይፋ የተነበበበት ተመሳሳይ ምክር ቤት) ለማንበብ የእምነት መግለጫ ጻፈ። እርሱ የሚከተለውን ጻፈ፦
ቅዱሳት ምሥጢራት ሁሉ ጸጋን ከመስጠት የራቁ በመሆናቸው እንኳ ጸጋን አያስተላልፉም ወይም አያከፋፍሉም ብዬ አምናለሁ፣ አዎ አውቃለሁ። በዚህ ጉዳይ፣ ኃያሉ ቄሳር ሆይ፣ ምናልባት እጅግ ደፋር ልመስል እችላለሁ። ነገር ግን አስተያየቴ ጸንቷል። ጸጋ የሚመረተው ወይም የሚሰጠው በመለኮታዊ መንፈስ ስለሆነ፣ ይህ ስጦታ የመንፈስ ብቻ ነው። በተጨማሪም፣ መንገድ ወይም ተሸካሚ ለመንፈስ አስፈላጊ አይደለም፣ ምክንያቱም እርሱ ራሱ ነገሮች ሁሉ የሚሸከሙበት ጉልበትና ኃይል ስለሆነ፣ መሸከም አያስፈልገውም፤ በቅዱሳት መጻሕፍትም እንደ ቅዱሳት ምሥጢራት ያሉ የሚታዩ ነገሮች ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በእርግጥ እንደሚሸከሙ አናነብም፣ ነገር ግን የሚታዩ ነገሮች ከመንፈስ ጋር ተሸክመው ከሆነ፣ የተሸከመው መንፈስ እንጂ የሚታዩ ነገሮች አይደሉም።
እንደ ዝዊንግሊ አባባል፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ውሃ ወይም እንደ ኅብስትና ወይን ያለ "መንገድ" ወይም "ተሸካሚ" አያስፈልገውም። በእነዚያ በኩል አይሠራም ነገር ግን ከእነርሱ ተለይቶ ይሠራል። እነርሱ መንፈስ ቅዱስን አይሸከሙም። አሁን በእርግጥ፣ መንፈስ ቅዱስ ለመሥራት መንገድ ወይም ተሸካሚ አያስፈልገውም። ነገር ግን ይህ በትክክል መጻሕፍት የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ለእኛ የሚያቀርቡበት መንገድ ነው። እኛ አካላዊ ሰዎች ስለሆንን በአካላዊ መንገዶችና መሣሪያዎች በኩል ለመሥራት ቃል ገብቷል። እምነትን የሚሰጠው የእግዚአብሔርን ቃል በመስማትና በጥምቀት ነው። ጳውሎስ ጥምቀትን "የዳግም ልደትና በመንፈስ ቅዱስ የመታደስ እና መታጠብ" ብሎ ይጠራዋል። ሐዋርያው ለኤፌሶን ሰዎች " ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ " (ኤፌ. 5፡25-26) ይላል፣ ይህም ማለት ቅዱስ ጥምቀት ማለት ነው። ጥምቀት ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የተዳመረ ውሃ ነው፣ ቃሉ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ እምነትን የሚሰራበት ምክንያት ነው።
ክርስቶስ በቃሉ ውስጥ ያዋሃደውን ለመለያየት ምንም አይነት ምክንያት የለም። ለኃጢአት ስርየት አንድ ጥምቀት አለ፣ እርሱም ከእግዚአብሔር የተስፋ ቃል "ንቁ ንጥረ ነገር" ጋር የተዳመረ የውሃ ጥምቀት ነው። ማንም ሰው ሁለት ጥምቀቶችን እንዲፈጥርና እግዚአብሔር ለድነታችንና ለመጽናናታችን ያዋሃደውን እንዲለያይ አትፍቀድ።
- ቄስ ጆሽ ሱሊቨን (Holy cross Lutheran church )
ትርጉም :- Augsburg Catholic