ወንጌል ሥጋዊ ፈውስን ተስፋ ይሰጣል?

By Pastor Josh Sullivan (translation:- Augsburg Catholic)

ወንጌል ሥጋዊ ፈውስን ተስፋ ይሰጣል?

ጥያቄ ፦ ብዙ የጴንጤቆስጤ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንደሚፈውሳቸው ካመኑ እያንዳንዱ ሰው እንደሚፈወስ ያምናሉ። ክርስቶስ ደግሞ ስለ በሽታችን ጭምር ሞቷል ይላሉ (ለምሳሌ ኢሳይያስ 53:4)። በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም (ለምሳሌ መዝሙር 103:3) ፈውስ የተሰጠ ተስፋ እንደሆነ ይናገራሉ። ስለ ጴንጤቆስጤ የፈውስ ትምህርት ምን ብለህ ትመልሳለህ?

መልስ ፦ የእምነት ፈውስ ከጴንጤቆስጤ “አራት ማዕዘን ወንጌል” (Foursquare Gospel) አራት ክፍሎች አንዱ ነው። ይህም የክርስቶስ መከራና ሞት ስለ ኃጢአታችን ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም በሽታና የሰውነት ሕመም ፈውስን እንደሚያስገኝ የሚያምን ትምህርት ነው። ለዚህ አረዳዳቸው ዋነኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኢሳይያስ 53:4-5 ሲሆን እንዲህ ይላል፦ “ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። ” ይህ አረዳድ በመዝሙር 103:3 ይደገፋል ተብሎ ይታሰባል፤ በዚያም ዳዊት እግዚአብሔርን “ ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥ ” ብሎ ያመሰግናል። አንዳንዶች ደግሞ የሥጋ ፈውስ ተስፋ በገላትያ 3:13 ውስጥ እንዳለ ያያሉ። ጳውሎስ “ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ ” ይላል፤ ከሕግ እርግማኖች መካከል አንዱ በዘዳግም 28:27 እንደተጠቀሰው በግብፅ ቁስል፣ በእባጭና በመቧጠጥ መመታትን ያካትታል። በአራት ማዕዘን ወንጌል ትምህርት መሠረት የሰውነት ፈውስ የኃጢአት ስርየት ያህል የወንጌል ክፍል ነው፤ ስለዚህም ፈውስ ካልተሰበከ ሙሉው ወንጌል እንዳልተሰበከ ተደርጎ ይቆጠራል፤ በሽታና ድካምም ካለ እምነት ደካማና እጦት ያለበት እንደሆነ ይታሰባል።የእምነት ፈውስ ትምህርት ዋነኛ ችግር ወንጌል መንፈሳዊ በረከቶችንም ሆነ ሥጋዊ በረከቶችን ተስፋ ቢሰጥም በተመሳሳይ መንገድ እንዳልሆነ ችላ ማለቱ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ በሽታዎቻችንን ተሸክሟል። በኢሳይያስ 53:4 “በእውነት ደዌያችንን ተሸክሞአል” ተብሎ በብዙ ትርጉሞች የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በሽታዎችን ያመለክታል። የነቢዩ ቃል እውነት ነው፦ “በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን።” ወንጌላዊው ማቴዎስ ኢየሱስ አጋንንትን እንዳወጣና ድውያንን እንደፈወሰ ሲጽፍ “በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፦ እርሱ ራሱ ድካማችንን ወሰደ በሽታችንንም ተሸከመ” ብሎ ተናግሮ ነበር (ማቴዎስ 8:17)። ነቢዩ አስቀድሞ እንደተነበየው የሥጋ ፈውስ የኢየሱስ አገልግሎት ክፍል ነበር። ኢየሱስ በማርቆስ 16:18 እንደተናገረው የሥጋ ፈውስ ደግሞ የሐዋርያት አገልግሎት ክፍል ነው። የኢየሱስ አገልግሎት ኃጢአትንም የኃጢአትን ውጤቶችም ያስወግዳል። ነገር ግን ወንጌል በዋነኝነት ከኃጢአት፣ ከበደልና ከዲያብሎስ ኃይል የሚያላቅቅ መንፈሳዊ ፈውስ ነው። ጌታ የእስራኤልን የኃጢአት ሁኔታ—እንዲሁም የመላውን የሰው ልጅ ሁኔታ—በኢሳይያስ መጀመሪያ ላይ እንደ በሽታ ይገልጸዋል። እንዲህ ይላል፦ “ ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል።ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም። ” (ኢሳይያስ 1:5-6)። በመስቀል ላይ ኢየሱስ ለሰው ልጅ ያስገኘው ፈውስ በዋነኝነት የመንፈሳዊ በሽታ ፈውስ ማለትም ከኃጢአት ነው።ወንጌል መንፈሳዊ በረከቶችን—የኃጢአት ስርየትን፣ መንፈስ ቅዱስን፣ የልጅነት ጸጋን፣ የአዲስ ሕይወት እድሳትንና የዘላለም ሕይወትን—ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተስፋ ይሰጣል። ኢየሱስ በማቴዎስ 7:7 “ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። ” ብሎ ያዝዘናል። በዮሐንስ 16:23 ደግሞ “ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። ” ይላል። ጸሎት እግዚአብሔር ተስፋ የገባቸውን ነገሮች መለመን ስለሆነ መንፈሳዊ በረከቶችን ያለ ቅድመ ሁኔታ ልንለምን ይገባናል። እነዚህን ነገሮች ሊሰጠን ፈቃዱ መሆኑን የምናውቀው በወንጌል ተስፋ ስለገባልን ነው። ጌታ ጸሎታችንን መስማት ብቻ ሳይሆን የምንለምነውንም እንደሚሰጠን ሙሉ በሙሉ በመተማመን እንለምናለን።

ወንጌል ደግሞ የዕለት እንጀራ የሚባሉትን ሥጋዊ በረከቶች—ይህን ሥጋና ሕይወት ለመደገፍ የሚያስፈልገንን ሁሉ—በቅድመ ሁኔታ ተስፋ ይሰጣል። ለሥጋ በረከቶች ስንጸልይ መጽሐፍ ቅዱስ በቅድመ ሁኔታ እንድንጸልይ ያስተምረናል። ለምሳሌ ዳዊት በአቤሴሎም አመፅ ምክንያት ከኢየሩሳሌም በሸሸ ጊዜ ለካህኑ ለሳዶቅ እንዲህ አለው፦ “ በእግዚአብሔር ዓይን ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆንሁ፥ መልሶ እርሱንና ማደሪያውን ያሳየኛል ፤ ነገር ግን። አልወድድህም ቢለኝ፥ እነሆኝ፥ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግብኝ አለው።” (2ኛ ሳሙኤል 15:25-26)። በማቴዎስ 8 ለምጻሙ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ።” አለው (ማቴዎስ 8:2)። ራሱ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ “ አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን ።” ብሎ ሲጸልይ ለሥጋ በረከቶች እንዴት መጸለይ እንዳለብን አስተምሮናል (ማቴዎስ 26:42)። ለጊዜያዊ በረከቶች፣ ለዚህ ሥጋና ሕይወት ለሚያስፈልገን ማንኛውም ነገር ስንጸልይ መጽሐፍ ቅዱስ በእምነት እንድንለምን፣ ጌታ ጸሎታችንን እንደሚሰማ እያወቅን ነገር ግን ፈቃዱ ከሆነ ብቻ እንድንለምን ያስተምረናል። ሐዋርያው ዮሐንስ በ1ኛ ዮሐንስ 5:14 “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል።” ብሎ ጽፏል። የእምነት ፈውስ ደጋፊዎች የሚሳሳቱት ወንጌል መንፈሳዊውንም ሆነ ሥጋዊውን በረከት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተስፋ ይሰጣል ብለው ስለሚያምኑ ነው።

ለሥጋ በረከቶች ጌታ ፈቃዱ ከሆነ ብቻ ምንጸልይበት ምክንያት ጌታ በእኛ ላይ እንዲመጡ የፈቀደላቸውና እምነታችንን ለመፈተን የሚጠቀምባቸው ስለሆነ ነው። ሰሎሞን በምሳሌ 3:11-12 “ልጄ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፥ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር።እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ።” ይላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በዕብራውያን 12 ላይ ጠቅሶ እንዲህ ይገልጻል፦ “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” (ዕብራውያን 12:11)። በሽታና የሰውነት ድካም እምነታችንን ለመፈተን ከሚላክልን ከእግዚአብሔር ተግሣጽ አንዱ ናቸው።

ማርቲን ኬምኒትዝ እንዲህ ይለናል፦ እግዚአብሔር የራሱ የሆኑትን በዚህ ሕይወት በመስቀልና በመከራ ማለማመድ ስለሚፈልግ፣ እኛም ለራሳችን ጥቅም ወይም ጌታ ደኅንነታችንን እንዴት እንደሚያሳድግ ስለማናውቅ፣ ክርስቶስ ስለ ዕለት እንጀራ ስንለምን ልንከተላቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን አዘጋጅቷል፦ በመጀመሪያ፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፤ ስለዚህም “ፈቃድህ ይሁን” እንላለን። ቀጥሎ፣ የምንለምነው ነገር ለጥቅማችንና ለደኅንነታችን የሚስማማ ከሆነ፤ ስለዚህም “ከክፉ ሁሉ አድነን” ብለን እንጸልያለን። በመጨረሻም፣ ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣ ከሆነ፤ ስለዚህም ጸሎታችንን “መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘላለም” በሚሉ ቃላት እንደመድማለን ። ስለዚህ ለዚህ ሕይወትና ለዚህ ሥጋ በሚመለከቱ ጉዳዮች ለእግዚአብሔር የተወሰነ መንገድ፣ ጊዜ ወይም ገደብ ልንደነግግለት አይገባንም፤ ይልቁንም ለፈቃዱ ራሳችንን አስገዝተን በልጅነት ታዛዥነት እንገዛለን ። ( Martin Chemnitz, Enchiridion, )

በሽታና ድካም በእኛ ላይ ሲመጣ፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፣ ለዘላለማዊ ጥቅማችን የሚያገለግል ከሆነ፣ ለእግዚአብሔር ክብርም የሚያመጣ ከሆነ በምሕረቱ እንዲያስወግድልን እንጸልያለን። እግዚአብሔር በተለምዶ በእርሱ አማካኝነት ፈውስን የሚሠራበት ስጦታ ስለሆነ የመድኃኒት ጥበብን እንጠቀማለን። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ስለ ሆድ ሕመሙ ትንሽ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ አሳስቦት ነበር (1ኛ ጢሞቴዎስ 5:23)። ኢሳይያስም በ2ኛ ነገሥት 20:7 ላይ በሕዝቅያስ እባጩ ላይ የበለስ ጥፍጥፍ እንዲቀመጥ አዘዘ። ዘመናዊ መድኃኒትን የእግዚአብሔር ስጦታና የፈውስ መንገድ አድርገን እንጠቀማለን፤ነገር ግን በእርሱ ብቻ ተማምነን አንኖርም ንጉሥ አሳ ጌታን ሳያማክር በሐኪሞች ብቻ እንደታመነው (2ኛ ዜና መዋዕል 16:12) ። እግዚአብሔር ድካማችንን ወዲያውኑ ወይም ጨርሶ በዚህ ሕይወት ውስጥ ካልፈወሰ፣ ይህ እምነታችን ደካማ መሆኑን አያመለክትም። ይልቁንም ይህ ለእኛ የእግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑን ያሳያል። እርሱ በላያችን ላይ የሚያኖረውን መስቀል በታዛዥነትና በደስታ እንድንሸከም መንፈስ ቅዱን ይሰጠናል ማለት ነው። የሚያስደስተው ከሆነ የሰውነታችንን መዳን ተስፋ በማድረግ መጸለያችንን እንቀጥላለን። እምነት በመከራችን ውስጥ “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ” (ሮሜ 8:28) ብለን እንድንናገር ያጽናናናል። እግዚአብሔር በሽታን፣ ደዌን፣ መከራንና ድካምን ለዘላለማዊ ጥቅማችን ይጠቀምባቸዋል። መታመም ወይም መድከም የደካማ እምነት ምልክት አይደለም። ይልቁንም እምነታችንን ይበልጥ ለመፈተን ከእግዚአብሔር የተሰጠ መስቀል ነው። በሽታና መከራ ውስጥ ጤና ማግኘት ላይ ብቻ ካተኮርን፣ እግዚአብሔር በበሽታውና በመከራው መካከል ሊሰጠን የሚፈልገውን ታላቅ በረከት እናጣለን።

Comments

Log in to join the conversation.

Log In

No comments yet — be the first to share your thoughts.